ሳሙኤል ኡምቲቲ ከባርሴሎና ጋር ለተጨማሪ አመታት ለመቆየት ኮንትራቱን አደሰ

በማንችስተር ዩናይትድ እንደሚፈለግ ሲነገር የነበረው ፈረንሳዊው ሳሙኤል ኡምቲቲ ለተጨማሪ አመታት ከባርሴሎና ጋር ለመቆየት ኮንትራቱን አደሰ።

የካታላኑ ቡድን ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ ካስፈረማቸው ተጫዋቾች ከቡድኑ ጋር በጊዜ የተዋሀደው ሳሙኤል ኡምቲቲ ነው ማለት ይቻላል።

ተጫዋቹ ኳስን በሚገባ ተረጋግቶ የሚጫወት በመሆኑ ከባርሴሎና  የአጨዋወት ጋር መስማማት ችላል።

ከሊዮን ወደ ባርሴሎና ሲዛወር የተቀመጠው የውል ማፍረሻ በወቅቱ ካለው የሌሎች ተጫዋቾች የውል ማፍረሻ አንፃር አነስተኛ በመሆኑ ሌሎች ክለቦች እንዳይወስዱት ተሰግቶ ነበር።

በተለይ ማንችስተር ዩናይትድ 60 ሚሊየን ዩሮ የውል ማፍረሻውን ከፍሎ ተጫዋቹን ለማስፈረም እንደሚፈልግ ሲነገር ቆይቷል።

ተጫዋቹ ባለፈው ሳምንት ከሌኪፕ ጋር በነበረው ቆይታ ኮንትራቱን ከባርሴሎና ጋር ማራዘም እንደሚፈልግ ከተናገረ በኋላ ዛሬ ማምሻውን ለተጨማሪ አምስት አመታት እስከ 2023 ድረስ ከቡድኑ ጋር እንደሚቆይ ይፋ ሆኗል።

ኡምቲቲ ወደ ባርሴሎና ከተዛወረ በኋላ 83 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን አንድ የላሊጋ እና ሁለት የኮፓ ዴልሬ ዋንጫዎችን ማግኘት ችሏል።

Advertisements