የጆሴ ሞሪንሆ የክረምቱ የመጀመሪያ ፈራሚ ዛሬ የህክምና ምርመራ እንደሚያደርግ ይጠበቃል

ማንችስተር ዩናይትድ ቡድኑን ለማጠናከር ከአለም ዋንጫው መጀመር ቀደም ብሎ የአንድ ተጫዋች ዝውውር ለማጠናቀቅ ዛሬ የህክምና ምርመራ ያደርጋል።

ባለፉት ሳምንታት ብራዚላዊው ፍሬድ ላይ ትኩረት አድርገው ሲሰሩ የነበሩት ቀያይ ሰይጣኖቹ በመጨረሻም ተጫዋቹን ለማስፈረም የመጨረሻው ምእራፍ ላይ ተገኝተዋል።

ዩናይትድ ለዝውውሩ 52 ሚሊየን ፓውንድ ለሻካታር ዶኔስክ የሚከፍል ሲሆን ዝውውሩን ለማጠናቀቅ ተጫዋቹ ዛሬ በካሪንግተን የልምምድ ማእከል የህክምና ምርመራ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

እንደ አንዳንድ መረጃዎች ከሆነ ደግሞ ፍሬድ ማምሻውን ከሊቨርፑል ተነስቶ ወደ ማንችስተር በማቅናት ቡድኑ የሚያርፍበት ሎውሪ ሆቴል እንደደረሰ ገልፀዋል።

የ 25 አመቱ ተጫዋች ከህክምናው በኋላም ለአራት አመታት በክለቡ የሚያቆየውን ስምምነት የሚያደርግ መሆኑን ነው ታላላቅ የመገናኛ ብዙሀን የገለፁት።

ተጫዋቹ ከብራዚል ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚገኝ በመሆኑ ትናንት አንፊልድ ላይ በአቋም መፈተሻ ጨዋታ ክሮሺያን ሲያሸንፉ 82ኛ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ገብቷል።

ከጨዋታው በኋላም ዝውውሩን በጊዜ አጠናቆ ወደ አለም ዋንጫው ላይ ትኩረቱን እንዲያደርግ ከብሔራዊ ቡድኑ ፈቃድ እንደተሰጠው ታውቋል።

የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ቲቴም ከጨዋታው በኋላ ተጠይቀው ተጫዋቹ ወደ ዩናይትድ የሚያደርገው ዝውውር እንደማያስገርማቸው በመናገር ዋናው ነገር ዝውውሩ ቶሎ መጠናቀቅ እንደሚገባው አስረድተዋል።

ፍሬድ አማካዩ ማይክል ካሪክ በጡረታ መገለሉን ተከትሎ የሱን ቦታን ለመተካት በሚል በጆሴ ሞሪንሆ የተመረጠ የክረምቱ የመጀመሪያ ፈራሚያቸው ይሆናል።

ተጫዋቹ 2013 ላይ ከብራዚሉ ኢንተርናሲዮናል ወደ ሻካታር ዶኔስክ ካቀና በኋላ በ150 ጨዋታዎች ላይ መሳተፍ ችሏል።

Advertisements