የዕለተ ማክሰኞ የአውሮፓ የዝውውር ወሬዎች

ወቅታዊ ትኩረቶች በሙሉ ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስት በሚጀመረው የዓለም ዋንጫ ላይ ቢያነጣጥሩም የአውሮፓ ሚዲያዎች በዕለቱ ይዘዋቸው የወጡ አበይት የዝውውር ወሬዎችም የእግርኳስ ዓለም ትኩረት እንደሆኑ ቀጥለዋል። ኢትዮአዲስ ስፖርትም የአውሮፓ አበይት አምስት ሊጎች የዕለቱ ዋነኛ የዝውውር ወሬዎችን እንደሚከተለው አሰናድታለች።

እንግሊዝ


ደ ኽያ በዩናይትድ “ደስተኛ” ነው

ዴቪድ ደ ኽያ ሪያል ማድሪድ ሊያስፈርመው ይፈልጋል የሚሉ ወሬዎች እንደአዲስ እየወጡ በሚገኙበት በዚህ ወቅት በማንችስተር ዩናይትድ “ደስተኛ” መሆኑን ተናግሯል።

ስፔናዊው ግብ ጠባቂ ወደበርናባው ሊዛወር ነው የሚሉ ወሬዎች ለረጅም ጊዜያት ሲናፈሱበት ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ተጫዋቹ ባለበት “ተረጋግቶ” መቀመጥ እንደሚፈልግ መናገሩን የዘገበው ጎል ድረገፅ ነው።

ሶክራቲስ ከማን ዩናይትድ ይልቅ አርሰናልን መርጧል

የዶርትሙንዱ ተጫዋች ሶክራቲስ ፓፓስታቶፖሎስ ወደአርሰናል ለመዛወር ሲል የማንችስተር ዩናይትድን ጥያቄ ውድቅ ማዳረጉን አባቱ ስለመግለፃቸው ጎል ድረገፅ ዘግቧል።

ጎል ድረገፅ የግሪካዊው ተጫዋች ዝውውር ለመጠናቀቅ መቃረቡን በመጋቢት ወር መጨረሻ ላይ ዘገበ እንደነበር አስታውሶ አሁን ደግሞ ተጫዋቹ በክረምቱ ዝውውሩን ለመቋጨት ወደለንደን መጓዙን ጨምሮ ገልፅዋል።

ኔይማር ከቶማስ ቱኸል ጋር ለመነጋገር በለንደን ይገኛል

ኔይማር የወደፊት ዕጣ ፈንታውን አስመልክቶ ከፒኤስጂው አዲስ አሰልጣኝ ቶማስ ቱኸል ጋር በለንደን እየተነጋገረ እንደሚገኝ ዘ ሰን ዘግቧል።

ብራዚላዊው አጥቂ ሃገሩ ከክሮሺያ ጋር ላደረገችው የወዳጅነት ጨዋታ በእንግሊዝ ይገኛል። እናም እንደጋዜጠው ዘገባ ቶኸልም በዚህ ሳምንት እንግሊዝ ገብተዋል።

ኔይማር ወደሪያል ማድሪድ ሊዛወር ነው በሚል ስሙ ከስፔኑ ክለብ ጋር ተያይዞ የሚገኝ ሲሆን የሁለቱ ስዎች ንግግርም የቀድሞው የዶርትሙንድ አሰልጣኝ የወደፊት ተስፋቸውን በክለቡ ለማቆየት ፍላጎት እንዳላቸው የሚያመላክት አስመስሎታል።

ዳሎት በማንችስተር የህክምና ምርመራ ሊያደርግ ነው

ዲያጎ ዳሎት ከፓርቶ ወደማንችስተር ዩናይትድ የሚያደርገውን ዝውውር ለማጠናቀቅ የህክምና ምርመራ ሊያደረግ እንደሆነ የስካይ ስፖርት ዘገባ አመልክቷል።

ቀያይ ሰይጣኖቹ የውል ማፍረሻው የሆነውን 17.5 ሚ.ፓውንድ ዋጋ በመክፈል የ19 ዓመቱን የመስመር ተከላካይ ለማስፈረም ፍላጎት እንዳለው ባለፈው ሳምንት የወጡ ዘገባዎች አመልክተው ነበር። እናም አሁን የተጫዋቹ ዝውውር በቀጠዮቹ ቀናት እንደሚጥናቀቅ ይጠበቃል።

አርስናል ፌላኒን ለማዘዋወር የሚደረገውን ፉክክር እየመራ ይገኛል

አርሰናል የማሩዋን ፌላኒን የዝውውር ስምምነት ፊርማ ለማግኘት የሚደረገውን ፉክክር በቀዳሚነት እየመራ እንደሚገኝ ታየምስ መፅሄት ዘግቧል።

ምንም እንኳ ማንችስተር ዩናይትድ የቤልጂየማዊውን ተጫዋች ስምምነት በአዲስ ኮንትራት ለማሰር ጥረት እያደረገ ቢገኝም እንዲሁም ኤሲ ሚላን ሌላኛው የተጫዋቹ ፈላጊ ሆኖ ቢመጣም መድፈኞቹ ግን ፉክክሩን በቀዳሚነት እየመሩ ይገኛሉ።

አዲሱ የአርሰናል አሰልጣኝ ኡናይ ኤምሬ ከዚህ ቀደም በፒኤስጂ የአሰልጥኝነት ዘመናቸው ተጫዋቹን ለማስፈረም ሙከራ አድርገው ነበር።

ስፔን


ሮናልዶ የ75 ሚ.ዩሮ ደመወዝ ጥያቄ አቀረ

ክርስቲያኖ ሮናልዶ በሪያል ማድሪድ የመቆየት ላይ እንዲደርስ አሁን ባለው ስምምነት ላይ 30 ሚ.ዩሮ የክፍያ ስምምነት ጭማሪ ያለው 74 ሚ.ዩሮ ዓመታዊ ደመወዝ እንዲከፈለው እንደሚፈልግ የካዴና ኮፔ ዘገባ አመልክቷል።

የፓርቱላዊው ተጫዋች ከሻምፒዮንስ ሊጉ የፍፃሜ ጨዋታ በኋላ ክለቡን ሊለቅ እንደሚችል ፍንጭ መስጠቱን ተከትሎ በማድሪድ የሚኖረው የወደፊት ዕጣ ፈንታ በእንጥልጥል ይገኛል።

እናም ተጫዋቹ እስከ2024 የሚዘልቅ እና በበርናባው እስከ39 ዓመቱ ድረስ ሊያቆየው የሚችል የስድስት ዓመት ኮንትራት እንዲቀርብለት ፈልጓል።

ሊቨርፑል ለኦብላክ ዝውውር 90 ሚ.ዩሮ አቀረበ

ሊቨርፑል የአትሌቲኮ ማድሪዱን ግብ ጠባቂ ያን ኦብላክን ለማስፈረም ያስችለኛል ያለውን 90 ሚ.ዩሮ የዝውውር ዋጋ ማቅረቡን የስፔኑ ጋዜጣ ዶን ባሎን ዘግቧል።

ቀዮቹ በሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ መጥፎ የሚባል አቋም ያሳየውን ሎሪስ ካሪዩስ ምትክ የሚሆናቸው ግብ ጠባቂ ያዛውሯሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኦብላክ የቀዮቹ የረጅም ጊዜ ዒላማ ሆኖ ቆይቷል። አሁን ደግሞ የርገን ክሎፕ ለተጫዋቹ ዝውውር የውል ማፈርሻውን 100 ሚ.ዩሮ ለመክፈል እንቅስቃሴ ጀምረዋል።

ግሪዝማን የባርሴሎና ጥያቄ ውድቅ ማዳረጉን ተናገረ

አንቱዋን ግሪዝማን ወደባርሴሎና መዛወር የሚችልበትን ዕድል ውድቅ በማድረግ በአትሌቲኮ ማድሪድ አዲስ ኮንትራት ለመፈረም መቃረቡን ለጓደኞቹ ስለመናገሩ የኤቢስ ስፓርት ዘገባ አመልክቷል።

ባርሴሎና የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቹን ዝውውር በ100 ሚ.ዩሮ ያጠናቅቃል ተብሎ ቢታሰብም፣ ነገር ግን ግሪዝማን የዓለማችን ኮከብ ባደረጉት ዲያጎ ሲሞኒ ስር እየሰለጠነ መቆየትን ምርጫው አድርጓል። አትሌቲኖ ማድሪድ ባለፈው ወር ያሸነፈው የዩሮፓ ሊግ ዋንጫ ተጫዋቹ በዋናዳ ሜትሮፓሊታኖ ለተማጨማሪ ጊዜያት በመጫወት ተጨማሪ የዋንጫ ክብሮችን ማግኘትን ምርጫው እንዲያደርግ ሳያደርገው እንዳልቀረም ታምኗል። ግሪዝማን አዲስ በሚፈርመው ኮንትራት የውል ማፍረሻ ስምምነቱን ከፍ በማድረግ የዓለማችን ከፍተኛ ተከፋይ የሚያደረገው እንደሆነም የኤቢሲ ዘገባ ጨምሮ አመልክቷል።

ኤቨርተን ለዊሊያን ጆሴ የዝውውር ጥያቄ የማቅረብ ፍላጎት አለው

የመርሲ ሳይዱ ክለብ ኤቨርተን ለሪያል ሶዴዳዱ የፊት ተጫዋች ዊሊያን ጆሴ የዝውውር ጥያቄ ለማቅረብ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ሙንዶ ዲፓርቲቮ ጋዜጣ ዘግቧል። ይሁን እንጂ ኤቨርተን 60 ሚ.ዩሮ የሆንውን የብራዚለዊውን ተጫዋች የውል ማፍረሻ መክፈል ይጠበቅታል።

ዶርትሙንዶች ባለፈው የውድድር ዘመን በ33 ጨዋታዎች 18 ግቦችን ማስቆጠር የቻለውን የ26 ዓመቱን ተጫዋች ለማስፈረም ፍላጎት ቢያሳዩም የሶሴዳድን የዝውውር ጥያቄ በማየት ወደኋላ ማፈግፈግን መርጠዋል።

ዊሊያን በስፔን የመቆየት ፍላጎት ያለው ቢሆንም፣ ነገር ግን ሶሴዳዶች የቡድን ስብስባቸውን የማስፋት ውጥን ያላቸው መሆኑን ተከትሎ እንዲሁም ከፕሪሚየር ሊጉ ክለብ ለተጫዋቹ የቀረበውን የደመወዝ ክፍያ ለመክፍለ የማይችሉ በመሆናቸው የቀረበላቸውን ጥያቄ ውድቅ ለማድረግ እንደሚቸገሩ ታምኗል።

ቼልሲና አርሰናል ሲሊሴንን ለማስፈረም የሚደረገውን ፉክክር ተቀላቀሉ

ቼልሲና አርሰናል የሊቨርፑል የዝውውር ዒላማ የሆነውን ኻስፐር ሲሌሰንን ልማስፈርም የሚደረገውን ፉክክር ተቀላቅለዋል። ነገር ግን ባርሴሎና ለግብ ጠባቂው ዝውውር 60 ሚ.ዩሮ ዋጋ እንዲቀርብለት ይፈልጋል። ሲሌሰን በ2016 ወደኑ ከምፕ ከተዛወረበት ጊዜ አንስቶ በክለቡ ከማርክ-አንድሬ ተር ሽቴገን ቀጥሎ በሁለተኛ ተመራጭ ግብ ጠባቂነት ሲያገለግል ቆይቷል። ይሁን እንጂ የ29 ዓመቱ ሆላንዳዊ የመጀመሪያ ተሰላፊነት ሚናን የማግኘት ጥብቅ ፍላጎት አለው። ቼልሲ በዚህ ክረምት ቲብዋ ኮርትዋን የማጣት ስጋት የተጋረጠበት ሲሆን፣ አርሰናልም በፒተር ቼክ የረጅም ጊዜ ቆይታ ላይ ስጋት እንዳለው የዘገበው ስፖርት ጋዜጣ ነው።

ጣሊያን


ሪያል ማድሪድ አሌግሪን ለመቅጠር ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀ

እንደቱቶስፖርት ዘገባ ከሆነ የሪያል ማድሪዱ ፕሬዝዳንት ፍሎረንቲኖ ፔሬዝ ባለፈው ሳምንት የጁቬንቱሱን አሰልጠኝ ማሲሚላኖ አሌግሬን ለመቅጠር ያልተሳካ ሙከራ አድርገዋል። ይሁን እንጂ ጣሊያናዊው አሰልጠኝ አንድ ቀን የበርናባውን ክለብ በአሰልጠኝነት ይመራሉ ተብሎ ይታመናል።

ፔሬዝ አርብ ዕለት ከጁቬ ጋር ግንኙነት አድርገው የነበረ ቢሆንም፣ ያገኙት ምላሽ ግን አሉታዊ ነበር። ነገር ግን ቢያንኮነሪዎቹ የቀድሞው አማካኝ ተጫዋቻቸው ዚነዲን ዚዳንን በአሰልጠኝነት ወደቱሪን የመመለስ ፍላጎት የሚኖራቸው ከሆነ ሪያሎች የ50 ዓመቱን አሰልጣኝ ለማግኘት በቀጣዩ ክረምት ዳግመኛ ወደጣሊያን ሊመለሱ ይችላሉ።

ጁቬንቱስ ሄጉዌንን ለመሸጥ እየጣረ ነው

ማሲሚላኖ አሌግሬ ፈጣን አጥቂ የሚፈልጉ በመሆናቸው ጁቬንቱስ ጎንዛሎ ሄጉዌንን ለመሸጥ ሙከራ እያደረገ ይገኛል።

እንደላ ስታምፓ ዘገባ ከሆነ የጣሊያኑ ሻምፒዮን የአርጄንቲናዊው ተጫዋች ምትክ በማደረግ አልቫሮ ሞራታን እና አንቶኒ ማርሺያልን በዝውውር ዒላማቸው ውስጥ አስገብተዋቸዋል።

አትሌቲኮ ማድሪድ እና ፒኤስጂ በሄጉዌን ላይ ፍላጎት ያላቸው ክለቦች ሲሆኑ፣ ጁቬንቱስም ለ30 ዓመቱ አጥቂ 60 ሚ.ዩሮ የዝውውር ዋጋ እንዲቀርብለት ይፈልጋል።

ሄጉዌን ከሁለት ዓመታት በፊት በ90 ሚ.ዩሮ ከናፓሊ ወደቱሪን ከተዛወረበት በኋላ በ105 ጨዋታዎች 55 ግቦችን ከመረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል።

ዌስትሃም ፊሊፔ አንደርሰንን ለማስፈረም ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀረ

የለንደኑ ክለብ ዌስት ሃም የላዚዮውን ተጫዋች ፊሊፔ አንደርሰንን ለማስፈረም ያቀረበው የ38 ሚ.ዩሮ የዝውውር ጥይቄ ሳይሳካ ቀረቷል።

የሴሪ አው ክለብ ለብራዚላዊው የአጥቂ አማካኝ 50 ሚ.ዩሮ የሚጠጋ የዝውውር ዋጋ እንዲቀርብለት የሚፈልግ ከመሆኑም በላይ የተጫዋቹን ዋጋ ከዚህም በላይ ከፍ ለማድረግ ተጫዋቹ በስታዲዮ ኦሎምፒኮ ያለውን ኮንትራት ስለሚያድስበት ሁኔታ ስምምነት እያደረገም ይገኛል።

ላዚዮ ተጫዋቹን በማንኛውም ዋጋ ለሌላ ክለብ የሚሸጥ ከሆነ ለቀድሞ ክለቡ ሳንቶስ የሽያጩን 25 በመቶ የመክፈል አስገዳጅ ስምምነትም አለበት።

ሞናኮ፣ ቼለሲና ዋትፎርድ ሌሎች የተጫዋቹ ፈላጊ ክለቦች መሆናቸውንንም የጋዜጣ ዴሎ ስፖርት ዘገባ አመልክቷል።

ጀርመን


ናጌልስማን የቀረበላቸውን ሪያል ማድሪድን የማስልጠን ዕድል ውድቅ አደረጉ

የሆፈኒየሙ አሰልጣኝ ኹሊያን ናጌልስማን የቀረበላቸውን ሪያል ማድሪን የማሰልጠን ጥያቄ ሳይቀበሉ መቅረታቸውን ቢልድ ዘግቧል።

ናጌልስማን ከማውሪሲዮ ፓቸቲኖ፣ የርገን ክሎፕ እና ማሲሚላኖ አሌግሪ ቀጥለው በፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ የአዲስ አሰልጠኝነት ቅጥር ዕጩ ዝርዝር ላይ ሰፍረዋል። ይሁን እንጂ አሰልጠኙ ምርጫቸው በሆፈኒየም መቆየት መሆኑን ገልፀዋል።

ኔገልስማን በክለቡ እስከ2021 ድረስ የሚቆይ ስምምነት ያለቸው ቢሆንም በቀጣዩ ክረምት ተግባራዊ የሚሆን የውል ማፍረሻ ስምምነት ግን የላቸውም።

የባየር ሙኒኩ ፕሬዝዳንት ስለሊቫንዶውስኪ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመናገር ፈቃደኛ አይደሉም

የባየር ሙኒኩ ፕሬዝዳንት ኡሊ ሄኔስ ስለሮበርት ሊቫንዶውስኪ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምለሳሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። የፓላንድ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቹ ባለፈው ሳምንት በወኪሉ በኩል የቡንደስሊጋውን ሻምፒዮን መልቀቅ እንደሚፈልግ መግለፁን ተከትሎ ቼልሲ፣ ማንችስተር ዩናይትድ፣ ፒኤስጂና ጁቨንቱስ ሁኔታውን በንቃት እንዲመለከቱት አድርጓቸዋል። ይሁን እንጂ ሆነስ ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጠዊ መግለጫ “አሁን ምንም የምንናገረው ነገር የለም።” ሲሉ ስለተጫዋቹ ጉዳይ ምላሽ ሳይሰጡ እንደቀሩ አበንድዜቱንግ ዘግቧል።

ባየር ሙኒክ ለሉካሲ ዲኜ የዝውውር ዋጋ ለማቅረብ አስቧል

የቡንደስሊጋው ሻምፒዮን ለባርሴሎናው የግራ መስመር ተከላካይ ሉካስ ዲኜ ዝውውር 17 ሚ.ዩሮ ዋጋ ለማቀርብ እያጤነበት እንደሚገኝ የኪከር መፅሄት ዘገባ አመልክቷል።

ሙኒክ በኮንትራቱ ላይ አንድ ዓመት ብቻ የቀረውን ስፔናዊውን የመስመር ተከላካዩን ኹሊያን በርናትን በዚህ ክረምት ለመሸጥ ዕቅድ ያለው መሆኑን ተከትሎ ምትክ ተጫዋች እያፈላለገ ይገኝል።

ባለፈው የውድድር ዘመን ስምንት የላ ሊጋ ጨዋታዎች ላይ ብቻ የመሰፍ ዕድል ያገኘው ዲኜ በኢንተር ሚላን እና ጁቬንቱስ የዝውውር ራዳር ውስጥም የሚገኝ ተጫዋች ነው።

ፈረንሳይ


ማኔ ሪያል ማድሪድን ለመቀላቀል ከስምምነት ላይ ደረሰ

እንደፈረንሳዩ ፍራንስ ፉትቦል ዘገባ ከሆነ የሊቨርፑሉ የፊት ተጫዋች ሳዲዮ ማኔ ሪያል ማድሪድን ለመቀላቀል ከስምምነት ላይ ደርሷል።

ምንም እንኳ በሁለቱ ክለቦች መካከል ምንም አይነት ስምምነት ባይኖርም ቀዮቹ በየትኛውም ዋጋ ተጫዋቹን የመሸጥ ፍላጎት እንደሌላቸው ነገር ግን ሴኔጋላዊው ተጫዋች አንፊልድን ለቆ ወደበርናባው ለመዛወር ደስተኛ መሆኑን የጎል ድረገፅ ዘገባ አመልክቷል።

ፒኤስጂ ለ16 ዓመት ተጫዋቹ አርትር ዛግሬ የፕሬፌሽናል ተጫዋችነት ኮንትራት አቀረበ

የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ፍላጎት ስጋት የገባው ፒኤስጂ ለ16 ዓመቱ የግራ መስመር ተከላካዩ አርተር ዛግሬ የፕሮፌሽናል ተጫዋችነት የኮንትራት ስምምነት አቅርቧል። ፒኤስጂ ሁለት ተጫዋቾቹ (የ18 ዓማቱ አማካኝ ክላውዲዮ ጎሜዝ ወደማንችስተር ሲቲ እና የ17 ዓመቱ የጨዋታ አቀጣጣይ ያሲን አድሊ ወደአርሰናል) ለመዛወር መቃረባቸውን እየተመለከተ ይገኛል።

ዛግሬ የሶስት ዓመት ስምምነት ያደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ወሬውን የዘገበው ለኪፕ አመልክቷል።

ኦሊቨር ለታንግ ቤን አርፋን ወደሬነ የመመለስ ፍለጎት አላቸው

የቀድሞው የፒኤስጂ የስፖርት ጉዳዮች ዳይሬክተር፣ ኦሊቪየ ለታንግ ሃቲም ቤናርፋን ወደሬነ የመውሰድ ፍላጎት እንዳላቸው ላ ፓሪሲያን ዘግቧል። ይሁን እንጂ የተጫዋቹ ደመወዝ ዝውውሩን እንዳይሳካ ሊያደረገው እንደሚችልም ለታንግ አልሸሸጉም።

ቤን አርፋ በፈረንሳይዋ መዲና ካሳለፈው ያለፍው አስቸጋሪ የውድድር ዘመን በኋላ በዚህ ወር መጨረሻ ከኮንትራት ነፃ ይሆናል።

ፒኤስጂን በ2017 የለቀቁት ለታንግ አሁን በሌላኛው የፈረንሳይ ክለብ ሬነ በፕሬዝዳንትነት እየሰሩ የሚገኙ ሲሆን፣ ከ30 ዓመቱ የቀድሞ የኒውካሰል የክንፍ ተጫዋች ጋር ንግግር አድርገዋል። ይሁን እንጂ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ምክኒያት ዝውውሩ ይሳካል ብለው አያምኑም።

Advertisements