ውዝግብ ፈጥሮ የነበረው የአርጄንቲናና የእስራኤል የወዳጅነት ጨዋታ መሰረዙ ተነገረ

አርጄንቲና ለ2018 የፊፋ ዓለም ዋንጫ ዝግጅት ከእስራኤል ጋር በእየሩሳሌም ከተማ ልታደርግ የነበረው ጨዋታ መሰረዙን አርጄንቲናዊው አጥቂ ጎንዛሎ ሄጉዌን ገልፅዋል።

ምንም እንኳ ስለጨዋታው መሰረዝ ከሁለቱም ሃገራት የእግርኳስ ማህበራት የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ ባይኖርም የጁቬንትሱ አጥቂ ሄጉዌን ግን የፊታችን ቅዳሜ ሊደረግ የነበረው ጨዋታ መሰረዙን አስረግጦ ተናግሯል።

“በመጨረሻ ትክክለኛውን ነገር አድርገዋል።” ሲልም ተጫዋቹ ለኢኤስፒኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ ገልፃዋል።

በተያያዘም የአርጄንቲና የእግርኳስ ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ሁጎ ሞያኖ ለራዲዮ 10 ተናግረውታል ብሎ ኢኤስፒኤን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ “በአርጄንቲና እና በእስራኤል መካከል የሚደረገው ጨዋታ መሰረዙ ጥሩ ነገር ይመስለኛል። ትክክለኛው ነገር ተደረጓል፤ ጥቅም የሌለው ነው። በእነዚያ ቦታዎች ላይ እየሆኑ ያሉ ነገሮችና የበርካታ ሰዎች መገደል እንደሰብዓዊ ፍጡር በማንኛውም መንገድ ልትቀበለው የምትችለው ነገር አይደለም። የተጫዋቾች ቤተሰቦች በሆኔታው ሃሳብ ገብቷቸዋል።” ሲሉ ገልፀዋል።

የወዳጅነት ጨዋታው ከስጋት የመነጨ ፍራታቻን ፈጥሮም ቆይቷል። ምክኒያቱ ደግሞ በሳምንቱ መጨረሻ ቀን የፍልስጤሙ የእግርኳስ ማህበር ዋና ኃላፊ ጂብሪል ራጁብ የአምስት ጊዜ የባሎን ዶር አሸናፊው ሊዮኔል መሲ በዚህ ጨዋታ ላይ የሚሰለፍ ከሆነ ደጋፊዎች የተጫዋቹን መለያና ምስል እንዲያቃጥሉ ጥሪ ማቅረባቸውን መናገራቸ ነበር።

ኃላፊው ጨምረው እንደገለፁት “እሱ ትልቅ ተምሳሌት ነው። ስለዚህ እሱን በግል ዒላማ እናደርገዋለን። እናም ሁሉም ምስሉን እና መለያውን እንዲያቃጥሉ እንዲሁም እንዲንቁት እንጠይቃለን።

የፍልስጤም እግርኳስ ፌዴሬሽን ዋና ኃላፊ ጂብሪል ራጁብ

“እኛም መሲ ይመጣል ብለን ተስፋ አናደርግም።” ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ጨምረው ተናግረዋል።

እንደኢኤስፒኤን ዘገባ ከሆነም በቴዲ ስታዲየም ሊደረግ የነበረው ጨዋታ የእየሩሳሌም ግዛት አካል በሆነችው ማልሃ አከባቢ የሚደረግ በመሆኑ እና ስፍራው እስራኤል ከ70 ዓመታት በፊት በጦርነት እንደሃገር ከመመስረቷ በፊት የቀድሞ የፍልስጤም ነዋሪዎች መንደር የነበረች መሆኗ በጨዋታው መደረግ ላይ በብዙዎች ዘንድ የውዝግብ መነሾ ሆኗል።

ይህ ከእስራኤል ጋር ሊደረግ የታቀደው የአቋም መለኪያ ጨዋታ አርጄንቲና ከሩሲያው የዓለም ዋንጫ ውድድር በፊት የምታደረገው የመጨረሻ ጨዋታ እንዲሆን የታቀደም ነበር።

Advertisements