1998 ፈረንሳይ – የፈረንሳዩ የአለም ዋንጫ ትውስታዎች

ፈረንሳይ አዘጋጅታ በሜዳዋ የተሞሸረችበት 16ኛው የአለም ዋንጫ የማይረሱ አጋጣሚዎች በአጭሩ ቀርበዋል።

በዚህ የአለም ዋንጫ ከእንግሊዝ፣ኮሎምቢያ እና ቱኒዚያ ጋር በአንድ ምድብ ውስጥ ትገኝ የነበረችው ሮማኒያ የምድቧን ሁለት ጨዋታዎችን በማሸነፍ መልካም ጅማሮ ማድረጓ ይታወሳል።

የጆርጅ ሀጂዋ ሩማኒያ የመጨረሻውን የምድቧን ጨዋታዋን ከቱኒዚያ ጋር ከማድረጓ በፊት ከግብ ጠባቂው በቀር [መላጣ ስለነበር]ሁሉም ተጫዋቾች ፀጉራቸውን ቀለም ተቀብተው ገብተዋል።

ይህን ያደረጉበት አንዱ ምክንያት ደግሞ በከፍተኛ ሞራል ላይ የነበረው ቡድን ይበልጥ ሜዳ ላይ ተጫዋቾቹ እርስበርስ እንዲግባቡ[በፀጉራቸው ተለይተው መቀባበል እንዲችሉ] እንደነበር ይታወሳል።

የሚገርመው የሩማኒያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾቹ ፀጉራቸውን ቀለም ከተቀቡ በኋላ ማሸነፍ ተስኗቸው ከዛ በኋላ ያደረጉት ጨዋታ ከቱኒዚያ ጋር አቻ ሲለያዩ በጥሎማለፉ ጨዋታ ደግሞ በክሮሺያ ተሸንፈው ከውድድሩ ውጪ መሆናቸው ነው።


ሎረንት ብላ እና ፋቢያን ባርቴዝ

ሁለቱ የፈረንሳይ ተጫዋቾች ከጫወታ በፊት የነበራቸው ልማድአይዘነጋም።ብላንክ ወደ ባርቴዝ በመጠጋት አብረቅራቂ መላጣውን የመሳም ልማድ ነበረው።

ይል ልማድ የመልካም እድል ምልክት በመሆን ብላንክ የባርቴዝን መላጣ እየሳመ እስከ ፍፃሜ ድረስ በመቀጠል ፈረንሳይ የአለም ዋንጫው አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል።

ሎረን ብላ ይህን ልማዱን በመቀጠል በዩሮ 2000 የአውሮፓ ዋንጫ ላይም የባርቴዝን መላጣ ሲስም እንደነበር ይታወሳል።


የዚዳን ማጂክ

ዚዙ የ1998 የፍፃሜ ጨዋታ ላይ ኮከብ ተጫዋች ነበር።አማካዩ ባልተለመደ መልኩ በፍፃሜ ጨዋታ ላይ ሁለት የጭንቅላት ጎሎችን ብራዚል ላይ በማስቆጠር ሀገሩ የዋንጫ ባለቤት ማድረግ ችሏል።

1998 ላይ ዋንጫን ያስገኘው የዚዳን ጭንቅላት በ 2006 የአለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ የማቴራዚ ደረት ላይ ማረፉ አይረሳም።


ትንሹ ማይክል ኦዌን

ለወትሮው ባላንጣ የሆኑት እንግሊዝ እና አርጀንቲና ባደረጉት የ 1998ቱ የአለም ዋንጫ ጨዋታ ላይ ማይክል ኦዌን በእንግሊዛዊያን ልብ ውስጥ መቅረት የሚታስችለው እንቅስቃሴ አድርጓል።

በወቅቱ 18ኛ አመቱ ላይ ይገኝ የነበረው ኦዌን አንድ ድንቅ ጎል ሲያገባ፣ቡድኑ ሌላ ጎል እንዲያስቆጥርም የፍፁም ቅጣት ምት በማስገኘቱ እንግሊዛዊያን ስሙን ጣሪያ አስነክተውት እንደነበር አይዘነጋም።

በዚህ ጨዋታ ላይ ሌላው የማይረሳው ዴቪድ ቤካም የአሁኑ የአትሌቲኮ ማድሪዱ አሰልጣኝ የሆነው ዲያጎ ሲሞኒ ላይ በሰራው ጥፋት በቀይ ካርድ የወጣበት እንዲሁም የካምቤል የጭንቅላት ጎል በዳኛው የተሻረበት ይገኝበታል።