ሞናኮ ቶማስ ሌማርን ለሌላ ክለብ ለመሸጥ መስማማቱን አሳወቀ

በአርሰናል እና በሊቨርፑል ሲፈለግ የነበረው ፈረንሳዊው ቶማስ ሌማር በቀጣዩ አመት ከሞናኮ ጋር እንደማይቀጥል ታውቋል።

ፈረንሳዊው አማካይ ሌማር ከሞናኮ የሚለያያው ቀጣዩ ኮከብ ተጫዋች መሆኑ እርግጥ ሆኗል።

ተጫዋቹ ከፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚገኝ ሲሆን ከአለም ዋንጫው በኋላ ከስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ይቀላቀላል።

ሞናኮ እና አትሌቲኮ ማድሪድ በተጫዋቹ ዝውውር ዙሪያ ላይ በመርህ ደረጃ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይፋ አድርገዋል።

በዝውውሩ ላይ የሚቀሩት የወረቀት ስራዎች ሁለቱ ክለቦች በቀጣይ ቀናቶች የሚያጠናቅቁ ይሆናል።

አትሌቲኮ ማድሪድ ለተጫዋቹ ያወጣው ሂሳብ ይፋ ባይሆንም አንዳንድ መረጃዎች ግን እስከ 63 ሚሊየን ዩሮ እንደሚከፍል ገልፀዋል።

ተጫዋቹ በአትሌቲኮ ማድሪድ የብሔራዊ ቡድኑ አጋሩ ከሆነው አንቶይን ግሪዝማን [ከክለቡ ጋር ከቆየ] ጋር የሚገናኝ ይሆናል።

ሌማር 2015/2016 ላይ ከኬን ወደ ሞናኮ ካቀና በኋላ ከክለቡ ጋር በፍጥነት በመዋሀድ የሊግ ኣ አንዱ ምርጥ ተጫዋች መሆን ችሏል።

በተጠናቀቀው የውድድር አመትም ለክለቡ 14 ጎሎችን ሲያስቆጥር 15 ኳሶችን ደግሞ ጎል እንዲሆኑ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።