ሪያል ማድሪድ አዲስ አሰልጣኝ መቅጠሩን አሳወቀ

በቅርቡ ከዚዳን ጋር የተለያየው ሪያል ማድሪድ ለቡድኑ አዲስ አሰልጣኝ መቅጠሩን አሳወቀ።

ሶስት ጊዜ በተከታታይ የአውሮፓ ቻምፕየንስ ሊግ ያሸነፈው ዜነዲን ዚዳን ሳይታሰብ ከማድሪድ ጋር የነበረው ቆይታ ማብቃቱን ካሳወቀ በኋላ አሰልጣኝ ሲያፈላልግ የቆየው ማድሪድ በመጨረሻም ተተኪ አሰልጣኙን አሳውቋል።

ስፔናዊው ጁለን ሎፔቲጉ ከአለም ዋንጫው በኋላ ማድሪድን የሚቀላቀሉ ሲሆን በክለቡም ለሶስት አመታት የሚቆዩ ይሆናል።

የወቅቱ የስፔን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሆኑት ሎፔቲጉ ቀደም ብለው ፖርቶን ለሁለት አመታት ካሰለጠኑ በኋላ 2016 ላይ የስፔን ብሔራዊ ቡድንን ተረክበዋል።

አሰልጣኙ 2003 ላይ የስፔን ከ 17 አመት በታች በማሰልጠን የጀመሩ ሲሆን ወደ ፖርቶ ከማቅናታቸው በፊት ከ 19፣ከ20 እና ከ 21 አመት በታች የስፔን ብሔራዊ ቡድንን ማሰልጠን ችለዋል።

አሰልጣኙ በአዲሱ ቤታቸው በባርሴሎና በሰፊ ነጥብ ተቀድመው ሶስተኛ ሆነው ያጠናቀቁበት የላሊጋ ውድድርን ማሸነፍ የመጀመሪያ የቤት ስራቸው ይሆናል።

እንደ ጋሪዝ ቤል አይነት ቆይታቸው ባልተረጋገጡ ተጫዋቾች ላይም ፈጣን ውሳኔያቸው ይጠበቃል።

ማድሪድ ማውሪሲዮ ፖቸቲኖ፣የርገን ክሎፕ ወይም አንቶኒዮ ኮንቴን እንደሚቀጥር ሲነገር እንደነበር ይታወሳል።