አንቶኒ ማርሻል ከማንችስተር ዩናይትድ መልቀቅ እንደሚፈልግ በወኪሉ በኩል አሳወቀ

የማንችስተር ዩናይትድ የመስመር ተጫዋች የሆነው አንቶኒዮ ማርሻል ከክለቡ መልቀቅ እንደሚፈልግ ተናገረ።

ማንችስተር ዩናይትድ በልዊ ቫንሀል ዘመን ከሞናኮ ያስፈረመው ወጣቱ ማርሻል ከኦልድትራፎርዱ ክለብ ጋር ያለው ቆይታ የሚራዘም አይመስልም።

ክለቡ የተጫዋቹን ኮንትራት ማራዘም ቢፈልግም በቂ የመሰለፍ እድል ያላገኘው ማርሻል ግን ከክለቡ ለመልቀቅ መዘጋጀቱን ታውቋል።

ተጫዋቹ በተለይ በመጀመሪያው አመቱ ድንቅ አጀማመር ያደረገ ሲሆን በደጋፊዎችም ሶስት ጊዜ የወሩ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ተመርጦ ነበር።

ነገርግን የጆሴ ሞሪንሆ ክለቡን መረከብ የእግርኳስ እድገቱ እንደ አጀማመሩ እንዳይሆን እንዳደረገው መናገር ይቻላል።

ጆሴ ተጫዋቹን በተደጋጋሚ ተጠባባቂ ወንበር ላይ በማስቀመጥ የጫወታ ጊዜው እንዲያንስ አድርገውታል።

በተለይ ደግሞ የአሌክሲስ ሳንቼዝ ወደ ክለቡ መዛወር የማርሻል የመሰለፍ እድል ይበልጥ እንዲቀጭጭ አድርጎታል።

በዚህም ምክንያት በራሺያው የአለም ዋንጫ ከሚሳተፈው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ምርጫ ውጪ መሆኑ ይታወሳል።

ተጫዋቹ ያሳለፈው ያልተሳካ አይነት አመት በድጋሚ ለመድገም ፍላጎት እንደሌለው በወኪሉ በኩል ተናግሯል።

ወኪሉ ፍሊፕ ላምቦሊ ለአንድ የፈረንሳይ መገናኛ እንደገለፀው ከሆነ ደምበኛው ማርሻል ከማንችስተር ዩናይትድ መልቀቅ እንደሚፈልግ ተናግሯል።

ጆሴ ልክ እንደ ዴብሩይን እና ሞ ሳላህ የሰሩት አይነት ስህተት በወጣቱ ማርሻል ላይ እንዳይሰሩ ተሰግቷል።