የዓለም ዋንጫ፡ ሩሲያ ከ ሳኡዲ አረቢያ፣ የጨዋታ ቅድመ ዳሰሳ

የ2018 የፊፋ ዓለም ዋንጫ አዘጋጇ ሃገር ሩሲያ በሞስኮው ሉዝህኒኪ ስታዲየም ሳኡዲ አረቢያን በምትገጥምበት ጨዋታ አንድ ብሎ ይጀምራል።

ሁለቱም ብሄራዊ ቡድኖች ይህን ጨዋታ የሚያደርጉት የነጥብ ባልህኑ ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ መጥፎ የሚባል አቋም በማሳየት ነው። ሩሲያ በጥር ወር ደቡብ ኮሪያን ከረታች ወዲህ ባደረገቻቸው ሰባት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ድል አልቀናትም፣ በአንፃሩ ሳኡዲ አረቢያ በተከታታይ ያደረገቻቸውን ሶስት የመጨረሻ የወዳጅነት ጨዋታዎች ተሸንፋለች።

ሩሲያ ከ2002 የዓለም ዋንጫ ወዲህ እንዲሁም ሳኡዲ አረቢያ ከ1994ቱ የአሜሪካኑ የዓለም ዋንጫ ወዲህ በውድድሩ ላይ የመጀመሪያ ድላቸውን ለመቀዳጀት ይህን የሉዝህኒኪን ጨዋታ በጉጉት ይጠብቃሉ።

ሩሲያ ከ ሳኡዲ አረቢያ
ቀን፡ ሐሙስ ሰኔ 7፣ 2010 ዓ.ም
ሰዓት፡ ምሽት 12፡00 (በኢትዮጵያ ሰዓት)
ሜዳ፡ ሉዝሂንስኪ ስታዲየም፣ ሞስኮ

ተጫዋቾቹ ስለጨዋታው ምን አሉ?

ፍዮዶር ስሞሎቭ (ሩሲያ)፡ [የሳኡዲ አረቢያ ብሄራዊ ቡድን] በቴክኒኩ ረገድ ሚዛናዊ የሚባል ቡድን ነው። ረጅምና አጭር ጨዋታ ይጫወታሉ። ጥሩ የኳስ ቁጥጥርም አላቸው። በአጥቂ ስፍራ ላይም ፈጣን ተጫዋቾች አሏቸው። አሰልጣኛቸውም ከቺሊ ነው። ጥሩ የኳስ ቅብብል ያለው ጨዋታ ለማድረግ ጥረት ሲያደረግ ልትመለከቱትም ትችላላችሁ።

ኦሳማ ሃውሰዊ (ሳኡዲ አረቢያ): “የዓለማችን ወሳኝ በሆነው ውድድር ላይ የመክፈቻው አካል በመሆናችን ደስተኞች ነን።

“በወዳጅነት ጨዋታዎች ላይ ከፍተኛ ብቃት አሳየናል። ከጀርመን ጋር ያደረገነው ጨዋታ (ባለፈው አርብ 2ለ1 የተሸነፉበት) ለዚያ ማሳያ ነው። እናም የሳኡዲ ቡድን ጠንካራው የእሲያ ተፎካካሪ ነው።

“ምኞታችንም እስከመጨረሻው ዙር ድረስ ለማለፍ ነው።”

ግምታዊ የመጀመሪያ አሰላለፎች

ሩሲያ: ኢጎር አኪንፊቭ፣ ማሪዮ ፈርናንዴዝ፣ ፌዶር ኩድሪያሾቭ፣ ሰርጌ ኢግናሼፊች፣ ዩሪ ዚርኮቭ፣ ሮማን ዞብኒን፣ ዳለር ኩዝያቭ፣ አላን ዛጎቭ፣ አሌክሳንደር ሳሜዶቭ፣ ፌዶር ስሞሎቭ

የሩሲያ ብሄራዊ ቡድን

ሳኡዲ አረቢያ፡ አብዱላህ አል-ማዩፍ፣ ኡሳማህ ሁሳዊ፣ ኦማር ሁሳዊ፣ ያሰር አል-ሻህራኒ፣ ሞሐመድ አልባሪክ፣ አብዱላህ ኦቲፍ፣ ሳልማን አልፋራጅ፣ ያህያ አል-ሺህሪ፣ ታይሲር፣ አል-ጃሲም፣ ሳሌም አል-ዶሳሪ፣ ፋሃድ አል-ሞላድ

የሳኡዲ አረቢያ ቡድን

ይህን ያውቃሉ?

የትኛውም አዘጋጅ ሃገር በዓለም ዋንጫ ውድድር የመልፈቻ ጨዋታ ላይ ሽንፈት ደርሶበት አያውቅም። በውድድሩ የተደረጉ የመክፈቻ ጨዋታዎች አዘጋጁ ሃገር ስድስት ጊዜ ድል ሲያደርግ፣ ሶስት ጊዜ ደግሞ በአቻ ውጤት ተለያይቷል።