አንቶይን ግሪዝማን በቀጣይ አመት የሚጫወትበትን ክለብ አሳወቀ

ባርሴሎናን ጨምሮ በሌሎች የአውሮፓ ታላላቅ ቡድኖች ሲፈለግ የቆየው የአትሌቲኮው የአጥቂ መስመር ተጫዋች የሆነው አንቶይን ግሪዝማን በቀጣይ አመት የሚጫወትበትን ክለብ ይፋ አድርጓል።

2014 ላይ ከሪያል ሶሴዳድ ወደ ማድሪድ አቅንቶ ለአትሌቲኮ ማድሪድ ፊርማውን ያኖረው አንቶይን ግሪዝማን በተደጋጋሚ ስሙ ከባርሴሎና ጋር ሲነሳ ቆይቷል።

በቅርቡም ክለቡ ሌሎች ታላላቅ ተጫዋቾች እንዲያስፈርም ጥሪ በማድረግ እንዲሁም የራሱን ቆይታ ከአለም ዋንጫው ጅማሮ በፊት እንደሚያሳውቅ ተናግሮ ነበር።

ተጫዋቹ ቃል በገባው መሰረት በቀጣይ አመት የሚጫወትበትን ክለብ ይፋ አድርጓል።

በዚህም መሰረት በቀጣዩ የውድድር መርሀግብር ይህ ፈረንሳዊ አጥቂ ቆይታውን አሁን በሚገኝበት ክለብ ውስጥ አድርጎ እንደሚቀጥል ነው ያሳወቀው።

አትሌቲኮ ቶማስ ሌማርን ለማስፈረም በዚህ ሳምንት ያሳወቀ ሲሆን ይህ ዝውውር ለግሪዝማን ቆይታ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ይታሰባል።

ግሪዝማን ከሀገሩ ልጅ ከሆነው ከቶማስ ሌማር ጋር በአትሌቲኮ ማድሪድ በቀጣይ አመት የምንመለከተው ይሆናል።

ተጫዋቹ የአንድ አመት ኮንትራት ማራዘሚያ ባለፈው ክረምት ከፈረመ በኋላ እስከ 2022 ድረስ በአትሌቲኮ የሚያቆየው ኮንትራት አለው።

በሁሉም ውድድሮች 112 ጎሎችን ከአትሌቲኮ ያስቆጠረው አጥቂ በአለም ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታውን የፈረንሳይ የአጥቂ መስመር እየመራ ቅዳሜ አውስትራሊያን ይገጥማል።