ዓለም ዋንጫ | ግብፅ ከ ኡራጓይ፡ የጨዋታ ቅድመ ዳሰሳ

በ2018 የሩሲያው ዓለም ዋንጫ የሁለተኛው ቀን ጨዋታ በምድብ ሀ ላይ የሚገኙትን አፍሪካዊቷን ሃገር ግብፅን እና የውድድሩ የሁለት ጊዜ ሻምፒዮኗን ደቡብ አሜሪካዊት ሃገሯን ኡራጓይን ያገናኛል።

ግብፅ ከ ኡራጓይ
ቀን፡ ሰኔ 8፣ 20010 ዓ.ም
ሰዓት፡ 9፡00
ሜዳ፡ ኢካትረምበርግ

ይህ ጨዋታ ለፈርኦኖቹ ከሶስት አስርት ዓመታት በኋላ በፊፋ ዓለም ዋንጫ ላይ ተሳትፎ የሚያገኙበት በመሆኑ ከፍ ያለ ግምት ይሰጠዋል። ግብፃውያኑ የትከሻ ጉዳት ገጥሞት የነበረው ኮከባቸው ሞሐመድ ሳላህን ጉዳት በቅርብ ሲከታተሉ ቆይታው በጨዋታው ላይ እንደሚሰለፍ አረጋግጠዋል። በመሆኑም የጨዋታው አብይ ትኩረታቸው በሊቨርፑሉ ተጫዋች ላይ ይሆናል።

የሁለት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ መሆን የቻለችው ኡራጓይም በመጀመሪያው የዚህ ውድድር ጨዋታዋም ግብፅን የምትፈትን ሃገር እንደምትሆን ትጠበቃለች። የደቡብ አሜሪካዋ ሃገር ባለፉት ሁለት የዓለም ዋንጫዎች ላይ አራት ውስጥ በመግባትና የመጨረሻ 16ን በመቀላቀል ኣስደናቂ ብቃት ማሳየት ችላለች። አብዛኞቹ ተጫዋቾችም ባለፈው የ2014 የብራዚል ዓለም ዋንጫ ላይ መሰለፍ ችለው የነበሩ ናቸው።

ግምታዊ አሰላለፎች

ግብፅ፡ ሞሐመድ ኤል ሼናውይ፣ አል ጋብሪ፣ አሊ ጋብር፣ አህመድ ሄጋዚ፣ አህመድ ፋቲ፣ ሞሐመድ አብደል ሻፊ፣ ታሪክ ሃመድ፣ ሞሐመድ ኤልኒኒ፣ ሞሐመድ ትሬዝጌ፣ አብዱላ ሰዒድ፣ ሮመድሃን ሶብሂ፣ ማርዋን ሞህሴን

ኡራጓይ፡ ፈርናንዶ ሙስሌራ፣ ጉሌርሞ ቫሬላ፣ ጆሴ ማሪያ ጎሜዝ፣ ዲያጎ ጎዲን፣ ማርቲን ካሴረስ፣ ናሂታን ናንዴዝ፣ ማቲያስ ቫሲኖ፣ ሮድሪጎ ቤንታንኩር፣ ጆርጂያን ደ አራስካኢታ፣ ኤዲሰን ካቫኒ፣ ልዊስ ስዋሬዝ

ይህን ያውቃሉ?

ኡራጓይ ከ48 ዓመታት በፊት በ1970 ማሸነፍ ከቻለች ወዲህ የዓለም ዋንጫ ውድድር የመጀመሪያ ጨዋታዋን አሸንፋ አታውቅም። በእነዚህ ጊዜያት ውስጥም ሶስት ጊዜ አቻ ስትለያይ ፡ሶስት ጊዜ ደግሞ ሽንፈት ደርሶባታል። እናስ ይህን ፋፅሞ የማትፈልገውን መራር እውነታ በኢካታሪንበርግ ስታዲየም ትለውጠው ይሆን?