አለም ዋንጫ 2018 – የሰዊዲኖቹ ስለላ እና የደቡብ ኮሪያዎቹ ታክቲክ

እየተካሄደ ባለው የራሺያ የአለም ዋንጫ አንዳንድ የሚሰሙ መረጃዎች አስገራሚ ሆነዋል።

በአለም ዋንጫው በምድብ ስድስት ላይ የተደለደሉት ስዊዲን እና ደቡብ ኮሪያ የምድባቸውን የመጀመሪያ ጨዋታ እርስበርስ አድርገው በስዊዲን 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል።

ስዊዲኖቹ ከአለም ዋንጫው ጅማሮ በፊት ሰላይ አዘጋጅተው ኮሪያዎችን ልምምድ የሚያደርጉበት ድረስ በመሄድ ሲሰልሉ ነበር።

የስዊዲኑ ሰላይ ኮሪያዎች ልምምድ በሚያደርጉበት አካባቢ ተከራይቶ ይኖር እንደነበር ታውቋል።

ታዲያ ኮሪያዎቹም የዋዛ አልነበሩም፣የስለላ መረጃው ቀድሞ ደርሷቸው ኖሮ በልምምድ ወቅት እንዲሁም በአቋም መፈተሻ ጨዋታቸው ላይ የስዊዲኖቹን ሰላይ ለማሳሳት አንድ መላ አዘጋጁ።

የቡድኑ አሰልጣኝ ሺን ታእ ዮንግ ስለላውን ለማክሸፍ የተጠቀሙበት ዘዴ ይናገራል “እኛ ለዚህ ስለላ የራሳችን ታክቲክ አዘጋጅተን ነበር።አውሮፓዊያን የኤሺያዎች ፊት እየተመሳሰለ ለመለየት እንደሚቸገሩ ስለምናውቅ እና የስዊዲን ሰላይ ለማሳሳት በልምምድ እና በአቋም መፈተሻ ጨዋታዎቻችን ላይ የተለያዩ ቁጠር ያለው ማሊያ ለተጫዋቾቻችን እየቀያየርን እናለብስ ነበር።” ሲሉ ተናግረዋል።

ኮሪያዎቹ በልምምድ ወቅት አራት የተለያየ ቁጥር ያለው ማሊያ እየቀያየሩ ተጫዋቾቻቸውን ያለብሱ እንደነበር ታውቋል።

በመጨረሻ ውጤቱ ግን ስዊዲኖችን የጠቀመ ነበር።ስለላው ጠቅሟቸው ይሆን?