አለም ዋንጫ – የኢራኑ ግብጠባቂ የአሊሬዛ ቤራንቫድ አስደናቂ የህይወት ጉዞ


የኢራኑ ግብጠባቂ አሊሬዛ ቤናርቫድ ከእረኝነት እስከ አለም ዋንጫ ግብጠባቂነት ያደረገው አስደናቂ የህይወት ውጣ ውረድ በአጭሩ ቀርቧል።

በካርሎስ ኪሮዥ ትመራ የነበረችው ኢራን ከፖርቹጋል ጋር 1-1 ከተለያየች በኋላ ጠንካራ ፉክክር ካደረገችበት የአለም ዋንጫው በክብር ተሰናብታለች።

በጨዋታው የክርስቲያኖ ሮናልዶን የፍፁም ቅጣት ምት ላዳነው ግብ ጠባቂው አሊሬዛ ቤራንቫድ ደግሞ ምሽቱ የተለየ ነበር።

ይህ ግብጠባቂ ከከብት አርቢ ቤተሰቦቹ የተገኘ ሲሆን የእግርኳስ ተጫዋች ለመሆን ብዙ ውጣ ውረዶች እና ፈተናዎች አሳልፏል።

የልጅነት ጊዜውን ከብቶች እየጠበቀ በሚያገኛት ትንሽ ጊዜ ደግሞ እግር ኳስ እና ዳል ፓራን [ረጅም ርቀት ድንጋይ መወርወር ያለበት ባህላዊ ጨዋታ]ይጫወት ነበር።

አጥቂ ሆኖ በሰፈሩ መጫወት ቢጀምርም በአንድ ወቅት ጓደኛውን ተክቶ ግብጠባቂ በመሆን ድንቅ ኳስ በማዳኑ ግብጠባቂ ሆኖ ለመቀጠል ምርጫውን አደረገ።

ከቤተሰቡ ጋር ይኖርበት የነበረው ገጠራማ መንደር ለሌሎች ስራዎች እንጂ እግርኳስ ድጋፍ የሚሰጠው ስፖርት ባለመሆኑ ቤራንቫድ ከአባቱ ተቃውሞ ይገጥመው ነበር።

አባት ልጃቸው በከብት ርቢው ላይ እንዲሰማራ ማሊያውን እና ጓንቱን እስከመቅደድ ደርሰው ነበር።12 አመት ሲሞላው ግን ህልሙን ለማሳካት ገጠሯ መንደሩ ትቶ ረግጦት ወደማያቀው ወደ ዋናው ከተማው ተሂራን ተሰደደ።

ምርጫ የለውም፣በአካባቢው የሚያውቀው ሰው ስለሌለ ህይወቱን በጎዳና ላይ ማድረግ ጀመረ።ስደተኞ ያድሩበት የነበረ በረንዳ ላይም መተኛት ጀመረ።

የመጣው ህልሙ የሆነው ስፖርት[እግርኳስ] ለመጫወት በመሆኑ ሙከራ ለማድረግ ባሰበበት ክለብ ካምፕ ያለበት በር ላይ እንደ ውሻ ኩርምት ብሎ ያደረበት ጊዜ ያስታውሰዋል።

ቤራንቫድ የሮናልዶን የፍፁም ቅጣት ምት ያዳነበት ክስተት

“አዎ በራቸው ላይ አድሬ ጠዋት ስነቃ ሰዎች ለማኝ መስያቸው ብዙ ሳንቲም አጠገቤ አገኛለው፣አስታውሳለው ለመጀመሪያ ጊዜ ባገኘሁት ሳንቲም ከብዙ ጊዜ በኋላ ጣፋጭ ምግብ በላሁበት።”በማለት ያስታውሳል።

ቁመቱ ጥሩ ስለነበረ የጠየቀው የሙከራ ጊዜ ተቀባይነት አገኘ።ሙከራውን እየደረገ ለኑሮ የሚሆነው ገንዘብ ለማግኘት የልብስ ፋብሪካ ተቀጥሮ በመስራት፣መኪና በማጠብ ህይወቱን ይገፋ ጀመር።

በመቀጠል በአንድ ፒዛ ቤት በአስተናጋጅነት ተቀጠረ።በአንድ እለትም የቡድን አሰልጣኙ ፒዛ ሊመገቡ ወደ ቤቱ አቀኑ ።ቤራንቫድ አሰልጣኙን ለማስተናገድ በማፈሩ ሄዶ ለመታዘዝ አልፈለገም።

የቤቱ ባለቤት ግን መታዘዝ እንዳለበት ሲያስገድደው ከማፈሩ የተነሳ ስራውን አቁሞ ሹልክ ብሎ ከቤቱ ወጥቶ ሳይመለስ ቀረ።

በመቀጠል ልምምዱን እየሰራ የመንገድ ፅዳት ስራ ተቀጥሮ መስራት ጀመረ።ናፋ በሚባል ቡድን ውስጥም ከ 23 አመት በታች ቡድን ውስጥ ለመካተት እድል አገኘ።

ተጫዋቹ በልጅነቱ በሀገሩ ይጫወት የነበረው ዳል ፓራን ይባል የነበረው ድንጋይ በረጅም ርቀት የመወርወር ባህላው ጨዋታ ግብጠባቂ ሆኖ በቀላሉ ኳስ ለቡድን አጋሮቹ እንዲወረውር በመርዳቱ ህይወቱ ከብዙ ፈተና በኋላ ህልሙ እንዲሳካ አድርጎታል።

ከ 2015 በኋላም ሀገሩን በግብ ጠባቂነት በማገልገል ለአለም ዋንጫ ከተሳተፈ በኋላ ከፖርቹጋል ጋር በነበረው ጨዋታ የኮከቡን የፍፁም ቅጣት ምት በመያዝ የማይረሳ እለትን አሳልፏል።

Advertisements