የአለም ዋንጫ – ለእናቱ ሲል በወጣትነቱ ከብሔራዊ ቡድኑ ጡረታ የወጣው ተጫዋች

በአለም ዋንጫው ላይ ተሳታፊ የነበረው ተጫዋች ለእናቱ ሲል ከብሔራዊ ቡድኑ በጡረታ ተገሏል።

ወላጆች ከአብራካቸው ለተፈጠሩት ልጆች ያላቸው እንክብካቤ እና ስስት ተነግሮ አያልቅም።ልጆችም እንዲሁ ለወላጆች ያላቸው ፍቅር ወደር የለውም።

ለልጆች ከህይወት ፈተናዎች አንዱ ከባዱ ነገር ወለጆቻቸውን ከአካባቢያቸው ሲያጡ ወይንም ሲታመሙ መመልከት ነው።

የኢራን ብሔራዊ ቡድን አጥቂ የሆነው ሳርዳር አዝሙን ከእናቴ ጤንነት የሚበልጥ የለም በማለት በ 23 አመቱ ከ ብሔራዊ ቡድኑ ጫማውን ሰቅሏል።

የወቅቱ የኢራን ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ስሙ ከፍ ብሎ ከሚጠሩት ተጫዋቾች ውስጥ አንዱ የሆነው ወጣቱ አጥቂ ሳርዳር አዝሙን በማጣሪያ ጨዋታዎች 11 ጎሎችን ለሀገሩ ማስቆጠር ችሎ ነበር።

በአለም ዋንጫውም ሀገሩ በክብር እስከተሰናበተችበት ድረስም በቋሚነት በሁሉም ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ተጫውቷል።

ነገርግን በሱ እና በቡድኑ ላይ ከአንዳንድ ሰዎች ይቀርቡ የነበሩት ያልተገቡ ትችቶች እና ስድቦች እናቱን ለከፋ ህመም ዳርጓቸዋል።

የእናቱ ህመምም ተጫዋቹን በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንዲገኝ በማድረጉ ከብሔራዊ ቡድኑ እና ከእናቱ ጤንነት አንዱን የግድ ለመምረጥ መገደዱን ይናገራል።

“አንዱን የግድ መምረጥ ነበረብኝ።ምርጫዬም እናቴን አድርጊያለው።” በማለት በ23 አመቱ ከብሔራዊ ቡድኑ ጫማውን መስቀሉን አሳውቋል።

Advertisements